የፍልሰት መረጃ በሚያመነጩ ተቋማትና በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት መካከል የፍልሰት መረጃን ለማጋራት የመግባቢያ ሥምምነትና ፕሮቶኮል ፊርማ ተደረገ፡፡
የሥምምነቱና ፕሮቶኮሉ መፈረም በሀገራችን የተበታተኑ፣ ተደራሽ ያልሆኑ፣ ያልተናበቡና የትንተና ሥራ ያልተከናወነባቸው መረጃዎችን ዘመኑ በሚጠይቀው አግባብ በማደራጀት ለሚፈለገው ጥቅም ለማዋል ይረዳል፡፡
እንዲሁም የፍልሰት መረጃን በአግባቡ ለማሰባሰብ፣ ለመተንተንና የብሔራዊ ፍልሰት ስታቲስቲክስ ለማመንጨት በተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሠራርን የሚፈጥር ነው፡፡
የመግባቢያ ሥምምነቱና ፕሮቶኮሉ የመንግሥት 10 ዓመት ዕቅድ፣ የተባበሩት መንግሥታት ዘላቂ የልማት ግቦች፣ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ቃል-ኪዳን፣ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ቃል-ኪዳን እና የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግሥታት አባል ሀገራት የፍልሰት መረጃዎችን በማጣጣም ለፖሊሲ ግብዓት፣ ለጥናትና ምርምር እንዲውልም ያስችላል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት እ.አ.አ በታህሳስ 2023 በ2ኛው የስደተኞች መድረክ ከገባቸው ስድስት ቃል-ኪዳኖች መካከል የስደተኞች መረጃን በብሔራዊ ስታትስቲክስ ሥርዓት ውስጥ እንዲካተት ማስቻል አንዱ ነው፡፡
በመሆኑም የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ለመግባቢያ ስምምነቱና ፕሮቶኮሉ ገቢራዊነት ልዩ ትኩረት በመስጠት አቅም በፈቀደ የገንዘብ፣ የቴክኒክና ቁሳዊ ድጋፍ የሚያደርግ ይሆናል፡፡
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከስደት ተመላሾችን የቅብብሎሽ ሥርዓት ለማጠናከር በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተዘጋጀውን የተመላሽ መቀበያ ማዕከልና ከስደት ተመላሾችን ለመመዝገብ የሚያስችል የመረጃ ቋት እንዲለማ አድርጓል።
የመረጃ ቋቱ በመንግሥት ባለቤትነት እንዲተዳደርና ሥራው በዘላቂነት ተግባራዊ ይሆን ዘንድ የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ድጋፍ በማድረግ የላቀ አስተዋፅዖ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ በቀጣይም ይህንና መሰል የአቅም ግንባታ ድጋፎችን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
የመግባቢያ ሥምምነቱና ፕሮቶኮሉ የተፈረመው በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት እና የፍልሰት መረጃን በሚያመነጩ አሥራ አንድ የመንግሥት ተቋማት ማለትም በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በሰላም ሚኒስቴር፣ በፍትህ ሚኒስቴር፣ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እና የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራምም ከፈራሚዎቹ መካከል ሲሆኑ፣ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ጽ/ቤት ለፊርማው የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ አድርጓል፡፡












