Search
Close this search box.

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የአሁኑ ትውልድ ለመጪው ትውልድ አረንጓዴ ዓለም ማቆየት እንዳለበት ጥሪ አቀረቡ

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የአሁኑ ትውልድ ለመጪው ትውልድ አረንጓዴ ዓለም ማቆየት እንዳለበት ጥሪ አቀረቡ

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የአሁኑ ትውልድ የአካባቢ ሚዛንን ለመጠበቅ የሚረዱ ዘርፈ-ብዙ ዛፎችን በመትከል ለመጪው ትውልድ አረንጓዴ ዓለም ማቆየት እንዳለበት ተናገሩ፡፡

አቶ ተመስገን መልዕክቱን ያስተላለፉት የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ኢትዮጵያ በ2ኛው ዓለም አቀፍ የስደተኞች መድረክ ቃል የገባችው የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ይፋ በተደረገበት ልዩ መርሐ-ግብር ላይ ነው፡፡

“የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን በማስተናገድ የገቡትን ቃል እየፈጸሙ ነው። ለስደተኞች ከለላ መስጠት ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነት ቢሆንም፣ ይህን ተከትሎ የሚመጡ ተግዳሮቶችን በርብርብ መፍታት ይገባል’’ ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን የዛሬው መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ እ.አ.አ በታህሳስ 2023 በስዊዘርላንድ – ጄኔቫ በተካሄደው 2ኛው ዓለም አቀፍ የስደተኞች መድረክ በአራት ዓመታት ውስጥ ስደተኞች በሚገኙባቸው አካባቢዎች አንድ መቶ ሚሊዮን ዘርፈ-ብዙ ችግኞችን ለመትከል የገባችው ቃል-ኪዳን በይፋ ማስጀመሪያ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ወ/ሮ ጠይባ አክለውም “ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የኃላፊነትና ጫና መጋራት መርህ በማክበር፣ ብዙ ስደተኞችን እያስተናገደች ነው። በመሆኑም ይህ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር በተፈጥሮ ኃብት ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስና የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት በጣም አስፈላጊ ነው’’ ብለዋል፡፡

በዛሬው ልዩ መርሐ-ግብር፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የስ.ተ.አ አመራሮችና ሠራተኞች፣ የተ.መ.ድ ኤጀንሲዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ አጋር ድርጅቶችና የስደተኛ ተወካዮች በታደሙበት ከ2,000 በላይ ዘርፈ-ብዙ ችግኞች ተተክለዋል፡፡

Share: