የስደተኞች የመታወቂያና የሌሎች ወሳኝ ኩነት አገልግሎቶች ዳግም ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2016(ኢዜአ)፦ለዓመታት ተቋርጦ የቆየው የስደተኞች የመታወቂያና የሌሎች ወሳኝ ኩነት አገልግሎቶች መስጠት ዳግም መጀመሩን የስደተኞች እና ተመላሽ አገልግሎት ገለጸ።
ከሁለት ዓመታት በፊት በአገሪቷ በነበሩ የተለያዩ ምክንያቶች ለስደተኞች ይሰጥ የነበረው የወሳኝ ኩነት አገልግሎቶች ተቋርጦ ቆይቷል።
የኢፌዴሪ የስደተኞች እና ተመላሽ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ብሩህተስፋ ሙሉጌታ፤ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ የስደተኞች የመታወቂያና ሌሎች ወሳኝ ኩነት አገልግሎቶች በድጋሚ ተጀምረዋል።
በአዲስ አበባ ለሚገኙ ስደተኞች ዳግም መሰጠት የተጀመረው አገልግሎት በቀጣይ ወደ ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚገኙ ስደተኞች ተደራሽ የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል።
የወሳኝ ኩነት አገልግሎቱ ተቋርጦ መቆየቱ ለስደተኞች አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩን አስታውሰው በድጋሚ መጀመሩ የነበረውን ችግር የሚፈታ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዓለም አቀፍ ህግና በኢትዮጵያ የስደተኞች አዋጅ መሰረት ኢትዮጵያ የስደተኞችን መብት በመጠበቅና ከለላ በመስጠት ድንጋጌዎችን በአግባቡ እየተገበረች መሆኑንም ገልጸዋል።
ስደተኞች የሚፈልጉትን አገልግሎት ለማግኘት የወሳኝ ኩነት መረጃ አስፈላጊ በመሆኑ በመሰጠት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም የመታወቂያ፣ የልደት፣ የጋብቻ፣ ፍቺ እና የሞት የምስክር ወረቀት በአገሪቱ ለሚገኙ ስደተኞች መሰጠት ተጀምሯል ብለዋል።









