Search
Close this search box.

ለስደተኞችና ተቀባይ ሀገራት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ጠየቀች

*****

ለስደተኞችና ተቀባይ ሀገራት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ጠየቀች

**EBC**እንደዘገበው፡

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ እና አጋሮች ጫና እና ኃላፊነትን በመጋራት መርህ ለስደተኞች እና ተቀባይ ሀገራት ተጨባጭ ድጋፍ እንዲያደርጉ ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበች።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽነር 74ኛው የሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ በስዊዘርላንድ – ጄኔቫ እየተካሄደ ነው።

በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በመድረኩ እየተሳተፈ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የስደተኞች ጥበቃ እና ራስን መቻል ላይ እየተሠሩ የሚገኙ ሥራዎችን አስመልክቶ የተመዘገቡ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ፈተናዎች እና በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራትን ወ/ሮ ጠይባ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በማስተናገድ ከባድ ኃላፊነት እየተወጣች መሆኗን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ፣ በቀጠናው ባለው ግጭት ወደ ሀገሪቱ እየተመሙ ካሉ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጋር ተያይዞ የተከሰተውን ሁኔታ መስመር ለማስያዝ የተቀናጀ የቀውስ ምላሽ ያሻል ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ እና አጋሮች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው፤ በቀጣይም ጫና እና ኃላፊነትን በመጋራት መርህ ለስደተኞች እና ተቀባይ ሀገራት ተጨባጭ አጋርነት እንዲያሳዩ መጠየቃቸውን ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Share: