Search
Close this search box.

በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችን ህይወት የማሻሻል የቃል ኪዳን ሰነድ ተዘጋጀ

በስዊዘርላንድ ጀኔቭ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የምታቀርበውን ስድስት አዲስ የቃል ኪዳን ሰነድ ለማጽደቅ የተዘጋጀ የከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችም ከማህበረሰቡ ጋር ተቆራኝተው መኖር የሚችሉበት የቃል ኪዳን ሰነድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

እኤአ በ2019 በተካሄደው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉባኤ ላይ አራት ቃል ኪዳኖችን በትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ በማዕድንና መሰል ዘርፎች በማቅረብ ውጤታማ ስራ ማከናወኗንም አስታውሰዋል።

በአራቱ ቃል ኪዳኖች ያስመዘገበችውን ስኬት በቀጣይ ታህሳስ ወር በሚቀርቡት ስድስት ቃል ኪዳኖች መድገም የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በታህሳስ 2023 በስዊዘርላንድ ጀኔቭ በሚካሄደው የዓለም የስደተኞች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የምታቀርበው አዲስ ቃል ኪዳን በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች ከማህበረሰቡ ጋር ተቆራኝተው መኖር የሚችሉበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድም ያላት ሚና የጎላ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን፤ ኢትዮጵያ በ26 የመጠለያ ጣቢያዎች ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የስደተኞች መብትና ጥበቃን ማስከበር የሚያስችል ተራማጅ የህግ ማዕቀፍ አዘጋጅታ ስደተኞችን እያስተናገደች መሆኑንም አብራርተዋል።

የስደተኞች ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው በመሆኑ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብር መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር የኢትዮጵያ ተወካይ አንድሪው ምቦጎሪ በኢትዮጵያ ያለውን የስደተኞች አያያዝ በቅርበት እንደሚከታተሉ እና እገዛ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢጋድ የጤናና ማህበራዊ ልማት ዳይሬክተር ማዳም ፈቲያ አልዋን፤ በበኩላቸው ኢጋድ በኢትዮጵያ የሚከናወነውን የስደተኞች አያያዝ ለመደገፍ ፈጣን የተግባር እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

Share: