ኢትዮጵያ ለስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ለምታደርገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና ሊቸራት እንደሚገባ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ አስታወቀ።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡሞድ፣ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ባርሃም ሳሊህ፣ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን እና የአጋር ተቋማት ኃላፊዎችና ተወካዮች በጀዊ ስደተኛ መጠለያ ማዕከል ጉብኝት አድርገዋል።
በጉብኝቱም በማዕከሉ ለስደተኞች የተመቻቹ የኑሮ ማሻሻያ እና የገቢ ማስገኛ ዕድሎችን ተመልክተዋል። ከእነዚህም ውስጥ የሳሙና ማምረት፣ የወዳደቁ ፕላስቲኮችን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል እና የልብስ ስፌት ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
በዚሁ ወቅት ኮሚሽነር ባርሃም ኢትዮጵያ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ተቀብላ መሠረታዊና ማህበራዊ አገልግሎቶችን በማቅረብ ከአጋር አካላት ጋር እየሠራች በመሆኑ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅናና ምስጋና ሊቸራት ይገባል ብለዋል።
ድርጅታቸው ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት ለስደተኞችና ለአስተናጋጅ ማህበረሰቦች የሚቀርቡ ድጋፎችን ለማጠናከር እንደሚሠራም ገልጸዋል።
ርዕሰ-መስተዳድር ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው፣ ክልሉ ለብዙ ዓመታት በሰብዓዊና ዓለም አቀፍ ሕጎች መሠረት ስደተኞችን በመቀበል እና በማስተናገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
ስደተኞች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በሠላም እንዲኖሩና በልማት ሥራዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ መንግሥትና አጋር ተቋማት በቅንጅት እየሠሩ መሆኑንም አስረድተዋል።
የልዑኩ አባላት በመጠለያ ማዕከሉ ችግኝ የተከሉ ሲሆን፣ የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ምንጭ:- (የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት)
















